ልጅዎ ከአስጠኚ ጋር በደህንነት እንዲማር
በ Temari.et ላይ ያለ እያንዳንዱ አስጠኚ ቤተሰቦች ከመቅጠራቸው በፊት በቡድናችን ይረጋገጣል፤ ከማመልከቱ በፊትም የሥነ ምግባር ደንቡን ይቀበላል። ስለ አስጠኚ ወይም ስለ ትምህርት የሚያሳስብዎ ነገር ካለ ከመተግበሪያው ወይም ከድረ ገጹ ሊያሳውቁን ይችላሉ።
Temari.et የሚያደርገው
በቦታው የሚነሳ የፋይዳ መታወቂያ ፎቶ
እያንዳንዱ አስጠኚ የፋይዳ ቁጥሩን ያስገባል፤ ሲያመለክትም የካርዱን ሁለቱንም ገጽ በመሣሪያው ካሜራ ያነሳል። ቅጹ ቀድሞ የተቀመጠ የካርድ ፎቶ አይቀበልም። የራሱን ፊት ፎቶም መሣሪያው ካሜራ ካለው በካሜራው ያነሳል፤ ከቡድናችን አንድ ገምጋሚም ፎቶውን ከካርዱ ጋር ያመሳክራል።
ከመጽደቁ በፊት ቃለ መጠይቅ
የ Temari.et ቡድን አስጠኚው በሚያስተምረው በእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት የጽሑፍ ፈተና ሊሰጥ ይችላል፤ ቃለ መጠይቅ ግን ሁልጊዜ ያደርጋል። በቃለ መጠይቁ አስጠኚው አጭር የሙከራ ትምህርት ያስተምራል፤ የልጆችን ደህንነት እንዴት እንደሚጠብቅም ይጠየቃል። አስጠኚው የሚጸድቀው ቃለ መጠይቁን ካለፈ በኋላ ብቻ ነው።
እያንዳንዱ ማረጋገጫ በመገለጫው ላይ
የአስጠኚው መገለጫ ላለፈው እያንዳንዱ ማረጋገጫ ምልክት ያሳያል፦ የፋይዳ መታወቂያውን፣ እያንዳንዱን ፈተና ከውጤቱ ጋር እና ቃለ መጠይቁን። ያላለፈው ማረጋገጫ በመገለጫው ላይ አይታይም።
የእያንዳንዱ ትምህርት መዝገብ
አስጠኚው እያንዳንዱን ትምህርት በ Temari.et ላይ ይመዘግባል፤ እርስዎም በሦስት ቀን ውስጥ ያረጋግጣሉ ወይም ችግር ያቀርባሉ። ችግር ያቀረቡበትን ትምህርት የ Temari.et ቡድን ለአስጠኚው ከመከፈሉ በፊት ያየዋል።
ቡድናችን ውይይትዎን የሚከፍተው በክርክር ወይም በደህንነት ስጋት ጊዜ ብቻ ነው
የ Temari.et ቡድን የአንድን ውል ውይይት መክፈት የሚችለው ከትምህርቶቹ በአንዱ ላይ የቀረበ ችግር ወይም ስለ ልጅ ደህንነት የቀረበ ስጋት ገና ክፍት እያለ እና ከተዘጋ በኋላ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ ብቻ ነው። በከፈቱ ቁጥር እንመዘግባለን። እርስዎ ወይም አስጠኚው ከውይይቱ ውስጥ አንድን መልዕክት ሪፖርት ካደረጉ፣ ያ መልዕክት ከሪፖርቱ ጋር ለቡድናችን ይደርሳል።
የደህንነት ስጋት ወዲያውኑ ለቡድናችን ይደርሳል
ስለ ልጅ ደህንነት የሚያቀርቡት ሪፖርት በጽሑፍ መልዕክት፣ በኢሜይል እና በመተግበሪያው በቀጥታ ለ Temari.et ቡድን ይደርሳል። ሪፖርቱን የሚያነበው ቡድናችን ብቻ ነው። ሪፖርት ላደረጉበት ሰው ማን እንደላከው አንነግረውም።
የአስጠኚዎች የሥነ ምግባር ደንብ
እያንዳንዱ አስጠኚ ማመልከቻውን ከመላኩ በፊት እነዚህን ደንቦች አንብቦ ይስማማባቸዋል። ደንቦቹን የጣሰ አስጠኚ በ Temari.et ላይ ያለውን ቦታ ሊያጣ ይችላል።
- ትምህርቶችን፣ መልዕክቶችንና ክፍያዎችን በ Temari.et ላይ ያድርጉ። ቤተሰብን በቀጥታ እንዲከፍልዎ በፍጹም አይጠይቁ።
- በሰዓቱ ይድረሱ፤ መምጣት ካልቻሉ ቤተሰቡን አስቀድመው ያሳውቁ።
- እያንዳንዱን ተማሪ በአክብሮት ይያዙ። ልጅን በፍጹም አይምቱ፣ አያሸማቅቁ ወይም አያስፈራሩ።
- በቤት ውስጥ ለሚሰጥ ትምህርት፣ ወላጅ ወይም ሌላ አዋቂ ሊያይዎት በሚችልበት ቦታ ያስተምሩ።
- ስለ ቤተሰቡ የሚያውቁትን በሚስጥር ይያዙ፤ የተማሪን ፎቶ በፍጹም አያጋሩ።
- የተስማሙበትን ያስተምሩ፤ እያንዳንዱን ክፍለ ጊዜ በታማኝነት ይመዝግቡ።
ስጋትዎን እንዴት ሪፖርት እንደሚያደርጉ
ስለ አስጠኚ ወይም ስለ ትምህርት የሚያሳስብዎ ነገር ካለ ከመተግበሪያው ወይም ከድረ ገጹ ለ Temari.et ቡድን ያሳውቁ። ሪፖርት ከማድረግዎ በፊት እርግጠኛ መሆን አያስፈልግዎትም። አስጠኚም ስለ ውል ወይም ስለ ስራ ማስታወቂያ ያለውን ስጋት በዚሁ መንገድ ሪፖርት ማድረግ ይችላል።
- ከአስጠኚው ጋር ያለዎትን ውል በ Temari.et መተግበሪያ ውስጥ ወይም ወደ temari.et ከገቡ በኋላ ይክፈቱ።
- ከውሉ አናት ላይ ስጋት ሪፖርት ያድርጉ የሚለውን ይጫኑ። በመተግበሪያው ውስጥ የጋሻ ምልክቱ ነው። ስለ አንድ ትምህርት ከሆነ ከትምህርቱ አጠገብ ያለውን የጋሻ ምልክት ይጫኑ።
- የሆነውን ይምረጡ። በዝርዝሩ ላይ የመጀመሪያው «የልጅ ደህንነት» ነው። ከቻሉ ጥቂት ቃላት ያክሉና ይላኩ።
- አስጠኚውን ገና ካልቀጠሩ መገለጫውን ከፍተው ከአናቱ አጠገብ «ሪፖርት ያድርጉ» የሚለውን ይጫኑ። በመተግበሪያው ውስጥ ባንዲራው ነው።
- አንድን መልዕክት ሪፖርት ለማድረግ በውይይቱ ውስጥ መልዕክቱን ተጭነው ይያዙ (በኮምፒውተር ላይ በቀኝ የማውስ ቁልፍ ይጫኑት)፤ ከዚያ «ሪፖርት ያድርጉ» የሚለውን ይምረጡ።
- ትምህርቱ አስጠኚው እንደመዘገበው ካልተካሄደ ትምህርቱን በውልዎ ውስጥ ከፍተው በሦስት ቀን ውስጥ «ችግር ያቅርቡ» የሚለውን ይጫኑ።
ከሰው ጋር ይነጋገሩ
አንድ ልጅ አሁን አደጋ ላይ ከሆነ መጀመሪያ ለፖሊስ በ991 ይደውሉ። የ Temari.et ቡድንን ለማግኘት «አግኙን» በሚለው ገጻችን ላይ ያሉትን ቁጥሮች ይጠቀሙ።